የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በስፖርት ዘርፍ የልዕቀት ማዕከል ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ተገለፀ!

የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የመማር ማስተማር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሙህራንን በማፍራት፣የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወንና ለአካባቢው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኝ ትልቅ የትምህርት ተቋም ነው።
የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በርካታ የትምህርት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ አንዱና የኮሌጁ የጀርባ አጥንት በሚል የተሰየመው የስፖርት ሳይንስ የትምህርት ክፍል ነው።
ይህ ትምህርት ክፍል በአራት ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ባላቸው የስፖርት ሳይንስ መምህራን እየታገዘ በየዓመቱ በመደበኛውና በማታው የትምህርት ፕሮግራም ከ150 በላይ የስፖርት ሳይንስ መምህራንን ያስመርቃል፣ የኮሌጁ መምህራን ለአካባቢው ህብረተሰብ ደከመኝና ሰለችኝ ሳይሉ የእውቀት፣የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ ሳይሰስቱ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
የእንጅባራ መምህራን ኮሌጅ እንደ ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ሁሉ ኮሌጁን በስፖርት ዘርፍ የልዕቀት ማዕከል( center of excellency) ለማድረግ ሌት ተቀን ደከመኝና ሠለቸኝ ሳይል በመስራት ላይ መሆናቸውን ለክልሉ ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ገልፀዋል።
ይህነንም መሰረት በማድረግ በግቢው ውስጥ ሁሉንም የስፖርት አይነቶች በሰርቶ ማሳያነት (Demonstration) የሚያገለግሉ እና በቀጣይም የአካባቢው ወጣቶች ትርፍ ጊዚያቸውን በስፖርት እየተዝናኑ የሚያሳልፉባቸው፣ በበርካታ የስፖርት አይነቶች ኢንተርናሽናል ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚችሉ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪይ ቦታዎች የተገነቡ ሲሆን አሁንም የስፖርት ሜዳዎችን የማስፋፋትና ደረጃቸውን የማሳደግ ስራ በማከናወን ላይ ናቸው።
ይህንንም አንቱ የተባለ ስራ የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በመጨረሻም ምልከታውን መሰረት አድርጎ በተደረገ ውይይት ኮሌጁ ከፍተኛ የሆነ አቅም ያለው ማሆኑና ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ክልሉ፣ ዞኑና ወረዳው የተለያዩ ስፖርታዊ ስልጠናዎችን፣ የወረዳ፣የዞን፣ ክልል አቀፍና ሀገር አቀፍ ውድድሮችን በማመቻቸተ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን የኮሌጁ ዲን ግልጸዋል።
ዲኑ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ጥራትና ብቃት ያላቸውን የስፖርት ሳይንስ ሙህራንን ለማፍራት እንዲቻል ስፖርት ኮሚሽን ከክልሉ ትም/ት ቢሮ ጋር በመነጋገር የዘርፉ ፎረም እንዲኖረው በማድረግ ዘርፉን የማሳደግ ስር ቢሰራ በማለት ምክረ-ሀሳባቸውን ለግሠዋል።
የተነሱትን ሀሳቦችና አጠቃላይ ምዕልከታውን መሰረት በማድረግ የኮሚሽኑ አመራርችና ክቡር ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በሚያስገርም ሁኔት መገንባታቸውን በመግለፅ ትልቅ የአካባቢው ህብረተሰብ በተለይም የወጣቱ መግልገያ ቋሚ ሀብት መሆኑን ገልፀዋል።
ክቡር ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ ቀጥለውም የኮሌጁ አመራሮችና መምህራን ተቀናጅታችሁ ይህን የመሰለ ትልቅ ተግባር መፈፀማችሁ ኮሌጁ ጥሩ ቁመና ላይ ያለ ስለመሆኑ የሚመሰክሩ ከመሆናቸውም በላይ የክልሉን ስፖርት አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያሳድጉ ተግባራት ናቸውና ይህንን በሁሉም ዘርፍ ተምሳሌትነት ያለውን ተግባር አጠናክራችሁ ቀጥሉ በማለት ከምስጋና ጋር በመግለፅ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን በማነኛውም ጊዜና ስዓት ከጎናቸሁ በመቆም የሚደግፍ መሆኑን በአፅንዖት በመገልፅ አመስግነዋል።